ጤናማ አስተሳሰብ ያለው ወጣት አዋዋሉም ጤናማ ነው

በሀገራችን፣ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ኤች አይ ቪን የተመለከቱ መረጃዎች የማስተላለፉ ተግባር መቀዛቀዙ ማኅበረሰባችን ለቫይረሱ የሚሰጠው ትኩረት እንዲቀንስ፣ ብሎም የቫይረሱ ስርጭት ቀንሷል ብሎ እንዲዘናጋ አድርጎታል፤ ኤች አይ ቪ ፈጽሞ ጠፍቷል ብለው የሚያስቡ ወጣቶችም ተፈጥረዋል፡፡ ይህ ደግሞ ቫይረሱ ድምጹን አጥፍቶ እንዲስፋፋ ምክንያት ሆኗል፡፡ በክልሎች፣ በተለይም የተለያዩ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች በሚካሄዱባቸው አካባቢዎች የቫይረሱ የሥርጭት መጠን ከፍተኛ ሲሆን፣ ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ ደግሞ አዲስ አበባ ከጋምቤላ ክልል በመከተል በቫይረሱ ስርጭት መጠን የሁለተኛ ስፍራን ይዛለች፡፡
ኤች አይ ቪ፣ የሀገራችንን ርዕይ ዕውን ለማድረግ ቁልፍ መሣሪያ ነው ተብሎ ተስፋ የተጣለበትን ወጣቱን የኅብረተሰብ ክፍል በይበልጥ ተጎጂ በማድረግ ምርትና ምርታማነትን በመቀነስ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖን ያሳድራል፡፡ የኢኮኖሚ ተጽዕኖው ከግለሰብ አንስቶ ወደ ቤተሰብና ሀገር ይሻገራል፡፡ የቫይረሱ ስርጭት የኢንቨስትመንትና የዕድገት ውጤቶችን የመሸርሸር ጫና ከማሳደሩም በተጨማሪ ያለችንን ውስን ጥሪት በልማት ላይ እንዳናውል ያደርጋል፡፡ የሚፈጥረው ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስም ቀላል አይደለም፡፡
ባለፉት ዓመታት ኤች አይ ቪ ኤድስን በሥራ ቦታዎች የመከላከል፣ የመቆጣጠርና ድጋፍና እንክብካቤ የማድረግ ተግባር በመንግሥት፣ በሠራተኛ ማኅበራት፣ በሲቪል ማኅበራትና በዓለም አቀፍ ተቋማት በስፋት ሲከናወን ቆይቷል፡፡ በዚህም፣ አበረታች ውጤቶችን ማስመዝገብ ተችሏል፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየተመዘገበ ያለው የቫይረሱ ሥርጭት መጠን መጨመርና ለቫይረሱ አጋላጭ የሆኑ ሁኔታዎች መስፋፋታቸው ደግሞ አዳዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ዜጎችን ቁጥር ለመቀነስ ከበፊቱ የተሻለ ጠንካራ ሥራ መሥራትን እንደሚያሻ የሚያመላክቱ ናቸው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን፣ ሀገራችን “በ2030 ኤድስን ማቆም” በሚል የያዘችውን ርዕይ ከግብ ማድረስም ሆነ ወጣቶችን ከቫይረሱ ተጋላጭነት መታደግ አይቻላትም፡፡
የዝግጅት ክፍላችን ያነጋገራቸው፣ በፌዴራል ኤች ቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አብርሐም ገብረመድህን፣ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የሚደረገው ጥረት ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት የሚችለው ከግለሰብ ጀምሮ እያንዳንዱ ዘርፍ ለጉዳዩ ትኩረት መሥጠት ሲችል ነው ይላሉ፡፡ ዳይሬክተሩ እንደሚናገሩት፣ የኤች አይ ቪን ጉዳይ ለጤናው ዘርፍ ብቻ የመተው አመለካከት ዛሬም ያልተቀረፈና የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ለሚደረገው ጥረት እንቅፋት እየሆነ ያለ ነው፡፡
የጤና ጉዳይ ከግለሰብ አመለካከት የሚጀምር መሆኑ ላይ የሚያሰምሩት ዳይሬክተሩ፣ እያንዳንዱ ሰው ጤናማ ዜጋ መሆን እንዲችል ለራሱ ከራሱ የበለጠ ኃላፊነት የሚወስድ አካል ሊኖር አይችልም፡፡ እንደ እርሳቸው ገለጻ፣ ሁሉም ግለሰብ ጤናውን ለመጠበቅ የሚረዳውን ግንዛቤ ሊይዝ የሚገባው መሆኑ እንዳለ ሆኖ፣ በተለይ ወላጆች ስለ ልጆቻቸው ጤና ግድ ሊላቸው ይገባል፡፡ ይህም ሲባል ወላጅ የልጆቹ አዋዋል ጤናማ መሆኑን መከታተል፤ አካሄዳቸው ለጤናቸው አስጊ በሚሆንበት ጊዜም መግራት ይኖርበታል፤ በራሱ ልጆች ብቻ ሳይወሰን በዙሪያው የሚገኙ ታዳጊዎችና ወጣቶችን ጤና የመጠበቅ ኃላፊነትም አለበት፡፡ ሌላው ኃላፊነት ሊወስድ የሚገባው አካል መንግሥት ሲሆን፣ ለአሠራር ምቹ የሆኑ ፖሊሲዎችን ከመቅረጽ ጀምሮ የማኅበረሰቡን ንቃተ ህሊና በማዳበር የዜጎችን ጤና የመጠበቅ ትልቅ ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡
ኤች አይ ቪ፣ በይበልጥ ተጎጂ እያደረገው ያለው ወጣቱን የማኅበረሰብ ክፍል እንደመሆኑ መጠን የቫይረሱን ስርጭት በመግታትና ጤናማ ዜጋ በማፍራት ረገድ የትምህርቱ ዘርፍ የማይተካ ሚና አለው፡፡ ከጠቅላላው የኢትዮጵያ ህዝብ ግማሽ ያህሉ ወጣት ሲሆን፣ አንድ ሶስተኛው፤ ማለትም 30 ሚሊየን የሚጠጋ ህዝብ ደግሞ በዩኒቨርሲቲዎቻችን ውስጥ ይገኛል፡፡ ይህም ዩኒቨርሲቲዎች ከሚሰጡት መደበኛ ትምህርት ባልተናነሰ፣ የወጣቱ ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንዳለባቸው ያመላክታል፡፡ ከዚህ አንጻር ዩኒቨርሲቲዎች የሚጠበቅባቸውን በአግባቡ መወጣት ከቻሉ፣ ስሜቱን የመግታት ዐቅም ያለው፣ ቤተሰቦቹና ሀገሩ ከእርሱ ብዙ እንደሚጠብቁ ኃላፊነት የሚሰማው፤ አስተሳሰቡ ጤናማ የሆነ ዜጋን ማፍራት ይቻላል፡፡
አስተሳሰቡ ጤናማ የሆነ ወጣት አዋዋሉም ጤናማ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ወጣቱ ለጤናው አስጊ በሆኑ አላስፈላጊ ቦታዎች ከመዋል እንዲቆጠብ በማድረግ ረገድ መምህራን ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ ኤች አይ ቪ የጤናው ዘርፍ ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የማኅበረሰብ ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ እያንዳንዱ ክፍለ ትምህርት ጉዳዬ ብሎ ሊመለከተው እንደሚገባም ያሳስባሉ፡፡
በሀገራችን ሁኔታ፣ ሴቶች የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ጫናዎች ያሉባቸው መሆናቸውን ያነሱት ዳይሬክተሩ በዚህ ሳቢያ ሴቶች ከወንዶች የበለጠ ለኤች አይ ቪ ተጋላጭ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡ ከዚሁ ጋር አያይዘውም፣ በሀገራችን የሴቶችን እኩልነት ለማረጋገጥ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ ማኅበራትና ተቋማት ተግባር ግቡን ሊመታ የሚችለው የሴቶችን ለኤች አይ ቪ ተጋላጭነት መቀነስ የሚያስችል ሥራ ሲሠሩ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ እንደ እርሳቸው ሀሳብ፣ የሴቶችን ለቫይረሱ ተጋላጭነት ለመቀነስ ከእነዚህ አካላት በላይ በባለቤትነት ሊሠራ የሚገባው አካል አይኖርም፡፡
የሀገራችን ኢኮኖሚ ማደግ የሚችለው ቫይረሱ እያሳደረ ያለውን ችግር ስፋትና ጥልቀት እያንዳንዱ አካል በውል ተረድቶ ለመፍትሔ መንቀሳቀስ ሲችል እንደሆነ አጽንዖት የሰጡት ዳይሬክተሩ፣ የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት የሚደረገው ጥረት ውጤት እንዲያመጣ ከተፈለገ የሕግ አውጪውን፣ ሕግ አስፈጻሚውና ሕግ ተርጓሚው አካል፣ መገናኛ ብዙኃንና የእያንዳንዱን ዘርፍ ተቀናጅቶ መሥራት ይጠይቃል ብለዋል፡፡ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የምንችለው ጤናው የተጠበቀ ዜጋ ማፍራት ስንችል መሆኑን ሁሉም ሊገነዘበው እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አብርሐም ገ/መድኅን
ዮርዳኖስ ፍቅሩ

Alarm: