ኮርፖሬሽኑ ከ16ሺ በላይ ሠራተኞችን የፀረ ኤች አይ ቪ መድሃኒት ተጠቃሚ እያደረገ ነው

ዮርዳኖስ ፍቅሩ
በሀገራችን የኤች አይ ቪ ኤድስን ስርጭት ለመግታት መላ ሕብረተሰቡን የማንቃቱ ተግባር ይበልጥ መጠናከር የሚገባውን ያህል፤ ይህ ንቅናቄ ሠራተኛውን ያማከለ ከማድረግ አኳያ ትኩረት እንዲሰጠው ማድረግም ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያት ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋለጭ ተብለው ከተለዩት የእድሜ ክልል ውስጥ የቀዳሚነትን ስፍራ የሚይዘው ወጣት አብላጫ ሰዓቱን ስራ ቦታ የሚያሳልፍ መሆኑ ነው፡፡
ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወጣት ካለበት ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ተዘዋውሮ የሚሠራ ሲሆን፣ ተንቀሳቃሽ፣ በኮንስትራክሽን ላይ የተሠማሩና፣ በትላልቅ የልማት ተቋማት ላይ የሚሠሩ ሠራተኞች ለኤች አይ ቪ ያላቸው የተጋላጭነት መጠን በወሲብ ንግድ ላይ ከተሰማሩ ሴቶች ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭትን በመግታት ዙሪያ የተቀረጹ ፕሮግራሞች ትግበራም የቫይረሱ ስርጭት በተለይም በተጠቀሱት የሥራ አካባቢዎች ላይ ያለው የስርጭት መጠን አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ከግንዛቤ በማስገባት ለቅድመ መከላከል ሥራ ትኩረት ሰጥቷል፡፡ ከአደጋ የተጠበቀ ጤናማና ምቹ የሥራ አካባቢ መፍጠር፣ በስራ ቦታ ልዩነት አለማድረግ፣ የመከላከሉ ተግባር ጾታ ተኮር መሆኑን ማረጋገጥ፣ ክብካቤና ድጋፍ ማድረግ እንዲሁም የምክክር ባሕልን ማዳበርም መርሆዎቹ ናቸው፡፡
እነዚህን መርሆዎች በመከተል በሥራ አካባቢ፣ በተለይም ተንቀሳቃሽ ሠራተኛውን ከኤች አይ ቪ ተጋላጭነት ከመታደግ አኳያ ከ60ሺህ በላይ ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞችን የሚያስተዳድረው የስኳር ኮርፖሬሽን የተቻለውን ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
በኮርፖሬሽኑ የኤች አይ መከላከልና መቆጣጠር ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ታደሰ ገብረ ጊዮርጊስ እንደሚናገሩት የኮርፖሬሽኑ ጤና ዘርፍ ኤች አይቪ አስመልክቶ እየሠራ ያለው ሥራ መከላከልን ማዕከል ያደረገ ነው፡፡ በኦሮሚያ ክልል አራት፣ በአማራ አንድ፣ በደቡብ አንድ፣ አፋር ሁለት፣ እንዲሁም በትግራይ አንድ በአጠቃላይ በ12 ሳይቶች ሠራተኞችን እያሠራ የሚገኘው ስኳር ኮርፖሬሽን በመከላከል ዘርፍ ከሚፈጥራቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች በተጨማሪ፣ በሚፈጠርላቸው ግንዛቤ ተመርምረው ውጤታቸውን ላወቁና ቫይረሱ በደማቸው ለተገኘ ሠራተኞች ድጋፍና እንክብካቤ የታከለበት የመድሃኒት አቅርቦት አገልግሎትም ይሰጣል፡፡ አገልግሎቱ በብዛት በፋብሪካዎቹ ውስጥ ባሉ የጤና አገልግሎት ሰጪዎች የሚሰጥ ሲሆን፣ በፋብሪካዎቹ ውስጥ ህክምና አገልግሎት ከሌለ ሠራተኞቹ ህክምናቸው አቅራቢያ በሚገኙ የመንግሥት ጤና ጣቢያዎች እንዲከታተሉ ይደረጋል፡፡ በዚህ ሂደትም እስካሁን ድረስ ፕሮጀክቶችን በሚያከናውንባቸው ሁሉም ክልሎች ለአንድ ሺ 681 ሠራተኞች የፀረ ኤች አይ ቪ መድሃኒት እያቀረበ ይገኛል፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ይደረግ የነበረው እንቅስቃሴ መቀዛቀዝ ወደ ኮርፖሬሽኑም ተጋብቶ እንደነበር የሚያወሱት አቶ ታደሰ፣ አሁንም በርካታ መሠራት ያለባቸው ሥራዎች ቢኖሩም የተሻለ መነቃቃት እንዳለ ይገልጻሉ፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ግን ከአመራሩ በኩል ያለው ቁርጠኝነት አናሳ መሆን የመከላከሉን ስራ የተሻለ ውጤታማ እንዳይሆን ማነቆ እንደሆነበት ሳያነሱ አላለፉም፡፡ ከዚሁ ጋር አያይዘው ኮርፖሬሽኑ ከሚያመርተው ስኳር ጎን ኤች አይ ቪም እንዳይመረት በየደረጃው ያለው የኮርፖሬሽኑ አመራር በሥሩ ለሚያስተዳድረው ሠራተኞች ኃላፊነት ወስዶ፣ እንዲህ ባሉ የስራ አካባቢዎች ሊኖር የሚችለውን ቫይረሱን ስርጭት ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት፣ የመከላከል ሥራውን በንቃትና ቁርጠኝነት ሊያግዝ ይገባል ብለዋል፤ የየክልሉ ጤና ቢሮዎችም የኮርፖሬሽኑንም ሆነ በሌሎች ፕሮጀክቶች የሚሠሩ ሰራተኞችን ተጋላጭነት ለመቀነስ የሚደረጉ የአቻ ለአቻ ውይይቶችን በግብዓት ሊደግፉ እንደሚገባና ለሥራ ወደ ክልላቸው ለሚመጣው ሠራተኛ ኃላፊነት ወስደው እንዲሠሩ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ሌላው ያነጋገርናቸው በኮርፖሬሽኑ፣ በወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ ውስጥ የሚገኘው የወንጂ ሆስፒታል ኤ አር ቲ ክሊኒክ፣ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የምክር አገልግሎት ባለሙያ አቶ ወንድሙ ማሞ እንዳሉን፣ በክሊኒኩ አማካኝነት እየተሠራ ያለው ሥራ ሁለት ዓይነት ሲሆን የመጀመሪያው የመከላከል ሥራ ነው፡፡ የመከላከሉ ሥራ ዋነኛ መሳሪያ ግንዛቤን በማስጨበጥ፤ ንቃትን በመፍጠር ሲሠራ፣ ሠራተኛው ባለበት አካባቢ፣ ቤት ለቤትና በስራ ቦታ ላይ በመሄድ ትምህርት እንዲደርሰው ይደረጋል፡፡ በተለይም ሠራተኛው ሰብሰብ ብሎ የሚገኝባቸው የማሳ ቦታዎች ለማስተማር ምቹ በመሆናቸው እነዚህ አካባቢዎችና ጊዜያት ተመርጠው እየተሠራባቸው ይገኛሉ፡፡
ባለሙያው እንደሚናገሩት፣ የአቻ ለአቻ ውይይቶችም ግንዛቤን ለማስፋት የተመረጠ ዘዴ በመሆኑ ሠራተኛው አንድ ለ20 እየተደራጀ ውይይቶችን ያካሂዳል፡፡ የምክክር መድረኮቹ ግንዛቤን በማስፋት ረገድ እየተጫወተ ያለው ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ከአቻ ለአቻ ውይይቱ በተጨማሪ በየሦስት ወሩ በዘመቻ መልክ ሠራተኛውን የማንቃት ሥራዎች ይሠራሉ፡፡ በተለይም ይህ ጊዜ ብዙዎች ተመርምረው ራሳቸውን እንዲያውቁ ተነሳሽነትን የሚፈጥርላቸው ነው፡፡ የሠራተኛው ተመርምረው ራሳቸውን የሚያውቁና ወደ ህክምና አገልግሎት የሚመጡ ሠራተኞች ቁጥር መጨመር እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ውጤት ማሳያ ነው ማለት ይቻላል ያሉት ባለሙያው ከመከላከሉ፤ ባሻገር ድጋፍና ክብካቤም ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት መሆኑንም ይናገራሉ፡፡ እርሳቸው እንዳሉት በድጋፍና ክብካቤ ዘርፍም ሆስፒታሉ መድሃኒት በማቅረብና ሌሎች ድጋፎችንም በማድረግ ለሠራተኛው ተደራሽ መሆን ችሏል፡፡ ኤች አይ ቪ በደማቸው ለሚገኙ ሠራተኞች፣ በተለይም ሴቶችና ልጆቻቸው የህክምና አገልግሎትና በቂ ነው ባያስብልም ሌሎችም ድጋፎችንም እያደረገ ይገኛል፡፡
በርካታ ተንቀሳቃሽ ሠራተኛን በሚያሰሩ እንደ ስኳር ኮርፖሬሽን ያሉ ትላልቅ ፕሮጀክቶች በዋናነት ከሚሠሩት የልማት ሥራ ባልተናነሰ መልኩ ለኤች አይ ቪ ኤድስ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው የሚያሳስቡት ባለሙያው፣ የእነዚህ ተቋማትም ሆነ የሀገር ምርትና መርታማነት ሊያድግ የሚችለው ጤናማ አምራች ዜጋ ሲኖር መሆኑን በመገንዘብ ለሠራተኞቻቸው ጤና መጠበቅ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው ይመክራሉ፡፡

Alarm: