ለኤች አይ ቪ መስፋፋት ምክንያት የሆነው ልማድና ሥርጭቱን ለመግታት የሚደረገው ርብርብ

ሰላማዊት ውቤ
በጋንቤላ ክልል ከሚገኙት አምሥት ብሔረሰቦች መካከል በተለይ አኝዋክ መዠንገርና ኮሞ ወንድና ሴት ወጣቶች ከ14 ዓመት ዕድሜያቸው ጀምሮ የራሳቸውን ጎጆ ቀልሰው የሚኖሩበት ባህል አላቸው፡፡ዞኖቹ በቋንቋ ቢለያዩም በባህልና በአኗኗር ተቀራራቢነት ያላቸው ናቸው፡፡ ይሄ ባህል ደግሞ እንደ ክልል በሁሉም አካባቢ ከዘመን ዘመን እየሰፋ የመጣና እጅግ ተወዳጅ እንደሆነ የክልሉ ነዋሪዎች ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ በአብዛኛው በዚህ ቱባ ባህል ጎጆውን የሚቀልሱት ወንዶች ቢሆኑም ሴቷ ወንዱን ተከትላ መሄዷና ከወንዱ ጋር በመጣመር በአንድ ጣራ ሥር መኖሯ የተለመደ ነው፡፡በባህሉ ጨዋታው ፣አብሮ ማምሸቱና መዳራቱም ሆነ መዛለሉ ነውርነት የለውም፡፡ ሁለቱ ጥንዶች በግብረ ሥጋ መጣጣማቸው የሚለካውም በዚህ ጎጆ ነው፡፡ግንኙነቱ ከጋብቻ በፊት ሆነም አልሆነም ጥንዶቹ እርስ በእርሳቸው ስለሚተማመኑና ፈልገው የሚያደርጉት በመሆኑ በተለይም ኤች አይቪ እንደ አገር መምጣቱና መስፋፋቱ ከታወቀ በኋላ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የኤች አይቪ ምርመራ አድርገው ስለሚያደርጉት በጤናቸው ላይም ሆነ በዘላቂ መልካም ግንኙነታቸው ላይ የሚያመጣው አንዳችም ተፅዕኖ አልነበረም፡፡
በተለይ ታዳጊዎች ከቤተሰብ ጥገኝነት የሚላቀቁበትና ለልጆች ከሚወጣ ማንኛውም ወጪ በብዙ መልኩ የወላጅ ሸክም የሚቀልበት በመሆኑም ያለው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ የላቀ ነው፡፡ይሁንና የጋንቤላ ከተማ ነዋሪዋ ወ/ሮ ጅሊና ኦኬሎ እንደሚሉት አሁን አሁን ይሄ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ባህል በብዙ መልኩ ለዛውን እያጣና ለኤች አይቪ ስርጭት መስፋፋት ምክንያት እየሆነ መጥቷል፡፡
ወንድና ሴት ወጣቶች እንደ ቀድሞ ጎጆ በመቀለስና የራሳቸውን ትዳርና ቤተሰብ መስርተው በትኩስ ጉልበታቸው ሀብት አፍርተውና ኢኮኖሚያቸውን አጎልብተው ከመኖር ይልቅ ከጋብቻ በፊት በሚደረግ ልቅ የግብረ ሥጋ ግንኙነትና ሌሎች አጋላጭ ችግሮች ለኤች አይቪ ቫይረስ እየተጋለጡበት ነው፡፡በጥንዶች ጎጆ ስም ከአንድ በላይ የወንድና ሴት ጓደኛ የሚያያዝባቸው፣ ጭፈራ ፣ዝላይና ሌላም ሌላም ወሲብ ቀስቃሽ ፊልምና ዋዛ ፈዛዛ ድርጊት የሚከናወንባቸው ከሆኑ ከረምረም ብለዋል፡፡ብዙ ወላጅ ይሄን አያውቅም፡፡ልጁ ውጭ ቢያድርና ከቤት ቢወጣም የራሱን ጎጆ ወደ የሚመሰርትበት ባህል የሚገባ ስለሚመስለው ቁጥጥርም አያደርግ፡፡
እንደ ወይዘሮዋ የእሳቸው ልጅ በዚህ ምክንያት ለኤች አይቪ ከተጋለጡት ወጣቶች አንዷ ናት፡፡ልጃቸው ከቤት መውጣት የጀመረችው በ14 ዓመቷ ነው፡፡ውላ ምታድርባቸው ጊዚያቶች ቀላል አልነበሩም፡፡በኋላ እንደደረሱበት ብዙ ጊዜ ጭፈራ ቤቶች ታዘወትር ነበር፡፡ከወንድ ጓደኛዋ ጋር በመሆን የአልኮል መጠጥና ዕፅ ትጠቀምና ወሲብ ቀስቃሽ ፊልሞችን ታይ ነበር፡፡በዚህ አጋጣሚ ጓደኛዋም ሆነ እሷ ከሌሎች ጋር ወሲብ ይፈጽሙ ነበር፡፡በዚህ የተነሳ በኋላ እሱ በቀለሰው ጎጆ በትዳር ቢጠቃለሉም ጎጆ መመስረት ያስችላል በተባለው ባህል ሰበብ በኤች አይቪ ከመያዝ አልዳኑም፡፡አሁን ላይ እንደ ጋንቤላ ክልል የኤች አይቪ ስርጭት ከፍ ለማለትና በርካታ ወጣት ሴትና ወንዶች በኤች አይቪ እየተያዙ ያሉት በዚሁ ባህል ሰበብ በመሆኑ ባህሉ ሊጎለብት ቢገባም ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የሚያመዝን ይሆናልና በጥንቃቄ መያዝን ይሻል፡፡
የጋንቤላ ክልል ጤና ቢሮ የኤች አይቪ መርሐ ግብር ቡድን አስተባባሪ አቶ ፈረደ ሞሲሳ እንደሚሉት የቫይረሱ ስርጭት እጅግ እየበዛ ያለው በመዠንገር ዞን ነው፡፡ምክንያቱ እዚህ አካባቢ ወጣቶች ከ14 ዓመት ዕድሜያቸው ጀምሮ ራሳቸውን ችለው ከቤት የሚወጡበት ሁኔታ መኖሩና ሕብረተሰቡ እንደሚለው አሁን አሁን ለኤች አይቪ ቫይረስ ስርጭት መባባስ ምክንያት መሆኑ ዕውነት ነው፡፡
አሁን ላይ ይሄ አኗኗርና ባህል ለኤች አይቪ እንደሚያጋልጥ ጥናቶች አመላክተዋል፡፡ሴቶችና ወጣት ልጆች ከቤተሰብ ወጥተው ለብቻቸው ጎጆ ቀልሶ የመኖር ጉዳይ ለስርጭቱ ምክንያት እንደሆነ ክልሉም ደርሶበታል፡፡
የጋንቤላ ክልል የኤች አይቪ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኦባን ኔል እንደገለፁልን ወንድ ወጣቶች ከ14 ዓመት በኋላ ከቤት የሚወጡና የራሳቸውን ጎጆ የሚመሰርቱበትን እንዲሁም ሴቶች ልጆቹ ከነዚህ ታዳጊ ወጣቶች ጋር አብዛኛውን ጊዜ የሚያሳልፉበትን ባህል ወላጅ በአጠቃላይ ቤተሰብና ማህበረሰቡ ችግር እንዳለው አድርጎ አይቆጥረውም፡፡
በዚህ የተነሳ የሚያደርገው ምንም አይነት ቁጥጥር የለም፡፡ ባህሉ ኤች አይቪ በአገራችንም ሆነ በክልሉ ባልነበረበት ሰዓት የመጣና የቆየ ማህበራዊ ሕይወትን የሚያጠናክር መሆኑ ለመዘናጋቱ አስተዋጾ አድርጓል፡፡ሁኔታው ከኤች አይቪ ስርጭት ጋር ሲታይ በዚህ ዘመን ሌላ ችግር መፍጠሩ ተረጋግጧል፡፡ከ14 እስከ 29 ዓመት ዕድሜ ያለው አምራች የህብረተሰብ ክፍል ለቫይረሱ እንዲጋለጥ በማድረግ በኩል ያለው ተፅዕኖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡በክልሉ ያለው የኤች አይቪ ኤድስ ስርጭት አሁን ላይ ወደ 4ነጥብ 8 ከፍ እንዲል ምክንያት ሆኗል፡፡ከ400ሺ የጋንቤላ ሕዝብ ብዛት አንፃር 4ነጥብ 8 ወይም 19ሺ200 ሕዝብ በኤች አይቪ ኤድስ መያያዝ እጅግ አስፈሪና አሳሳቢ ነው፡፡
ይሄን ስርጭት መግታት የሚቻለው በጽሕፈት ቤቱ ወይም በጤና ቢሮ ብቻ በሚደረግ ርብርብ አይደለም፡፡አመራሩ ከክልል እስከ ቀበሌ እንዲሁም ሕብረተሰቡና ወላጅ ችግሩን ችግሬ ብሎ መያዝና መረባረብ ግድ ይለዋል፡፡አሁን ላይ ከክልል እስከ ቀበሌ አመራሩና ማህበረሰቡ ተቀናጅቶ በዋንኛነት ለቫይረሱ ስርጭት ምክንያት መሆኑ ከተረጋገጠውና በተለይ ወጣቱ ጎጆ ከሚወጣበት ባህል ጋር በተያያዘ የባህርይ ለውጥ እንዲያመጣ እየተሰራ ነው፡፡

Alarm: