የአቻ ለአቻ ውይይትና ትምህርት አገልግሎት በደብረ ብርሐን

ሰላማዊት ውቤ
ደብረ ብርሐን ከተማ ውስጥ ልዩ ሥሙ ካታንጋ በሚባለው መንደር በሴት አዳሪነት የሚተዳደሩ ሴቶች ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ታዲያ ይህን አጋላጭ ሁኔታ ለመቀነስ ከሚደረግ ጥረት ውስጥ በግልፅነት የታጀበ ውይይት አንዱ ነው፤
አንዷ የምታቀውን ሌላዋ ላትገነዘብ ትችላለችና ነው፡፡
ይህ ክፍተት በውይይት ለዚያውም ከአቻነት በመነጨ ውይይት ሲሞላ ለኤች አይ ቪ የመጋለጥ መጠን በእጅጉ ይቀንሳል ተብሎ ይታሰባል፡፡ በዚያ በተለምዶ ካታንጋ ተብሎ በሚባለው ሰፈር ያሉ ሴቶችም ይህን በመረዳት ይመስላል፤ ሥራ ከበዛባቸው በወር አንዴ ወይም በ15 ቀን አንዴ፤ ካልበዛባቸው በሳምንት አንድ ቀን የመወያያት ልምድ አዳብረዋል፡፡
ከዚህ መንደር ነዋሪ አንዷ የሆነችውና በውይይቱ አዘውትራ የምትሳተፈው ብዙ ጊዜም ውይይቱን የምትመራው ሥሟ እንዳይገለፅ የፈለገችን አንዲት ሴት በጉዳዩ ላይ አነጋግረናት ነበር፡፡ ጓደኞቿ ሱዚ እያሉ ይጠሯታል፡፡ ነገር ግን ይሄ ትክክለኛ ሥሟ እንዳልሆነና ከፈለግን ሱዚ ብለን ልንጠራት እንደምንችል በነገረችን መሠረት ሱዚ ብለን እንጥራትና ወጋችንን እንቀጥል፡፡ ሱዚ እንዳጫወተችን በመንደሩ ውስጥ እሷን ጨምሮ በሴት አዳሪነት የተሰማሩት ሴቶች የአቻ ለአቻ ውይይትና ትምህርት አገልግሎት ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡
ብዙ ጊዜ ውይይቱን የምትመራው እሷ ናት፡፡ እሷ በማትኖርበት ጊዜ ደግሞ በዕለቱ እኛ ልናገኛት ያልቻልነው ሌላዋ የመንደሩ ነዋሪ ትመራዋለች፡፡
ውይይታቸው በተለይ በዋናነት ራስን ከኤች አይ ቪ/ ኤድስ መከላከል ላይ ያጠነጥናል፡፡ ሱዚ እንዳወጋችን ታዲያ በውይይቱ ከሚነሱት ሀሳቦች መካከል ኮንዶምን በአግባቡና በጥንቃቄ መጠቀም ቅድሚያ ይሰጠዋል፡፡ ነገር ግን በአብዛኛው በውይይቱ እንደሚነሳው ሁሉም ኮንዶምን በአግባቡና በጥንቃቄ አይጠቀሙም፡፡
አብዛኞቹ ደንበኛቸው ከፍተኛ ብር ከሰጣቸው ያለ ኮንዶም ግንኙነት ያደርጋሉ፡፡ ጥቂቶቹ ደንበኞቻቸው አጠቃቀሙን ስለማያውቁ ግንኙነት እያደረጉ ኮንዶሙ የመፈንዳት ችግር ይገጥማቸዋል፡፡ በመንደሩ በነዚህ ምክንያቶች ብቻ በኤች አይ ቪ የተያዙ አሉ፡፡ መንደር ውስጥ ከነዋሪው የሚደበቅ አንድም ነገር ስለሌለ በውይይቱ በሌሎች ሴቶች ጉዳዩ ተነስቶም ቢሆን ውይይት ይደረግበታል፡፡ ሁሉም ሊባል በሚችል መልኩ አብዛኞቹ በግልጽ ውይይቱን ያደርጋሉ፡፡ እንደ ሱዚ በሴት አዳሪነት ሥራ የተሰማሩ ሴቶች ፈጥረው በተናገሩት የውሸት ሥም እንኳን ቆየት ብለው ቢጠሯቸው የማያስታውሱ እጅግ ድብቅ ቢሆኑም እርስ በእርሳቸው ሲሆን ውይይቱ በግልጽ እንዲናገሩ ይገፋፋቸዋል፡፡
ውይይቱ ብዙ ጥቅሞች ሲኖሩት በተለይ ራስን ለማወቅ የሚደረግ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ምርመራ ለማድረግ፤ በኤች አይ ቪ የተያዙት ደግሞ መድኃኒታቸውን በተገቢው መንገድ በመውሰድና ሕክምና በመከታተል እንዲኖሩ የሚያስችል ነው፡፡ በዚህ መንገድ ተጠቃሚ ከሆኑት አንዷ ሱዚ ናት፡፡ በአቅራቢያዋ በሚገኝ ጤና ተቋም ከሚሰጡ የጸረ-ኤች አይ ቪ አገልግሎቶች ጋር በማስተሳሰር ውይይቱን ጥሩ ውጤት እያገኘችበት ነው፡፡
በዚሁ ሥራ የተሰማራችው ወሰኔ ገብሬ እንዳለችን ደግሞ ከዚህ ቀደም ብዙ ሴቶች በተለይም በቫይረሱ የተያዙት ወንዶችን ደንበኞቻቸውን ወደ መበቀል የሚገቡበት አጋጣሚ ሰፊ ነበር፡፡ እነሱ በቫይረሱ የተያዙት መቼና በማን እንደሆነ ባያውቁም አብዛኞቹ በደንበኞቻችን ነው የተያዝነው ብለው ስለሚያስቡ ለብቀላና ወንዶችን ለማስያዝ ሲሉ ከሁሉም ጋር ግንኙነት የሚያደርጉት ያለ ኮንዶም ነበር፡፡ በኮንዶም ለሚጠይቃቸውም ፈቃደኛ የማይሆኑበት አጋጣሚ ሰፊ ነበር፡፡ ተስፋ በመቁረጣቸውና ለሌላው የማሰብ ግንዛቤ ያላቸው ባለመሆኑ እጅግ ጨካኞች ሆነው ነበር፡፡ ውይይቱ ይሄን ሁሉ ችግር ማስወገድና በሴቶቹ ዘንድ ግንዛቤ መፍጠር ችሏል፡፡ ይህ ውይይት በፈጠረው የግንዛቤ መዳበር በቫይረሱ በአዲስ የሚያያዙ ሴቶች ቁጥር ቀንሷል፡፡ ለሌላው ሕብረተሰብም በተለይም ለዘወትር ደንበኞቻቸው የማሰብ ልምድ እንዲያዳብሩም ውይይቱ እራሱን የቻለ አስተዋፅዖ አድርጓል፡፡
ከደብረ ብርሐን ከተማ አሥተዳደር ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ መፃሕፍት ቤት ጋር በመቀናጀት እነዚህ የሕብረተሰብ ክፍሎች አቻ ለአቻ ውይይቱን እንዲያደርጉ ከበስተጀርባ ሆኖ ድጋፍ የሚያደርገው የደብረ ብርሐን ዩኒቨርሲቲ የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ኃይማኖት ቢችል እንደገለጹልን የአቻ ለአቻ ቡድን ውይይት ተጋላጭ ሴቶች ያሉባቸውን አካባቢዎች በመለየትና ብዛታቸውንም በማጥናት በአቻ ቡድኖች እንዲደራጁና በአቻ ለአቻ ውይይት ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ ተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎችን መድረስ ከሚያስችሉ የባህርይ ተግባቦት ስልቶች አንዱ ነው፡፡
ዩኒቨርሲቲው ይሄንኑ በማሰብ ውይይቱ እንዲካሄድ መሥራቱን የጠቀሱት ዳይሬክተሯ የአቻ ለአቻ ውይይትን ተከትሎ በሚፈጠር ግንዛቤ የተለያዩ አገልግሎቶችን መጠቀም ፍላጎት የሚጨምር እንደሆነም ይናገራሉ፡፡ በመሆኑም በአቅራቢያ በሚገኙ ጤና ተቋም ከሚሰጡ የጸረ-ኤች አይ ቪ አገልግሎቶች ጋር የአቻ ለአቻ ትምህርት አገልግሎቱን በማስተሳሰር ተሳታፊዎች የተሟላ የፀረ-ኤች አይ ቪ አገልግሎትን እንዲያገኙ እየተሠራ መሆኑንም አጫውተውናል፡፡
እኛም አልን፤ በተለይም በተለያዩ የውጭ ድጋፎች እየተከናወኑ ያሉት ተጋላጭ ሴቶችን በተለይም ሴት አዳሪዎችን ለመድረስ የሚያስችሉ የባህርይ ተግባቦት አገልግሎቶች እየቀነሰ ካለው ድጋፍ አንፃር እንዳይቋረጡ በአገር ውስጥ ድጋፍ የሚመለከታቸው ዘርፎች ሲቪል ማህበራትና ሌሎች በመቀናጀት የሚሰሩበትን አሰራር ማጠናከር ትኩረት ይሻል፡፡ የአቻ ለአቻ ትምህርት በራሱ በቂ ባለመሆኑ በአገልግሎቱ የሚዳረሱ ሴቶች የገቢ ማስገኛ ሥልጠና እና የገንዘብ ድጋፍ እያገኙ ከኢኮኖሚ ተጋላጭነት እንዲወጡ ማድረግም ግድ ይላል፡፡
በተጨማሪም የአቻ ለአቻ ትምህርቱ ሂደት በሚፈጥርላቸው ግንዛቤ ምክንያት የአገልግሎቱ ተጠቃሚነት ፍላጎት ስለሚፈጠር በተሳለጠ የሪፈራል ቅብብል በአቅራቢያ የሚገኝ ጤና ተቋም የኤች አይ ቪ ምርመራና ምክር፣ አባላዘር ህመሞች ምርመራ፣ የቤተሰብ ምጣኔ፣ የፀረ-ኤች ኤቪ ሕክምናን ያካተተ የተሟላ የኤች አይ ቪ መከላከልና ሕክምና አገልግሎቶችን እንዲያገኙ የማድረግ አሠራሩ በየደረጃው ሊጠናከር ይገባል፡፡
ይሄም አቻ ለአቻ መሪዎችን ከተመረጡት ጤና ተቋማት ጋር በማስተሳሰር ሊከናወን ሚችል ሲሆን በተጨማሪም የተለዩት ተገላጭ የማህበረሰብ ክፍሎች በሚገኙባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የተመረጡ ጤና ተቋማት ጋር በማስተሳሰር ሊከናወን ሚችል ነው፡፡ የአገልግሎት አሰጣጡንም በየወቅቱ እየገመገሙ ማሻሻል ይገባል፡፡

Alarm: